የሀገር ውስጥ ዜና

ደህንነቱ የተጠበቀ የአየር ትራንስፖርት እንዲኖር ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር እንሰራለን – ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)

By amele Demisew

December 10, 2024

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ደህንነቱ የተጠበቀ እና ውጤታማ የአየር ትራንስፖርት እንዲኖር ከዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ድርጅቶች ጋር በትብብር እንሰራለን ሲሉ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት እና የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን 80ኛ አመት በዓል

በስካይላይት ሆቴል በአውደርዕይና ልዩ ልዩ ፕሮግራሞች እያከበረ ነው፡፡

በሥነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ ደህንነቱ የተጠበቀና እና ውጤታማ የአየር ትራንስፖርት እንዲኖር ከዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት እና አባል ሀገራት ጋር በቁርጠኝነት ትሰራለች፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግስቴ በበኩላቸው÷ በዓሉን ስናከብር በወቅቱ ሊታለም እንኳን ስለማይችለው የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ግንዛቤ ኖሯቸው ኢንዱስትሪው በኢትዮጵያ እንዲጀመር መሰረት ለጣሉ ቀደምት አባቶች ምስጋና ልናቅረብ ይገባል ብለዋል፡፡

በዓሉ ታሪክን ለመዘከር ብቻ ታስቦ የተዘጋጀ አይደለም በማለት ገልጸው፤ ኢትዮጵያ በመጪው ዘመን የምትጎናፀፈውን ብሩህ የስኬት ዘመንና አጠቃላይ የዓለም የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ የእድገት ጉዞን ለማጤን ጭምር ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዕለቱ “የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቱ በአፍሪካ እርስ በርሱ ያለው ቁርኝት ያሉት ጠቀሜታዎችና ፈተናዎች እንዲሁም የወደፊት ተስፋ ሰጪ ሁነቶች” በሚል ሲምፖዚየም የተካሄደ ሲሆን የፓነል ውይይቶችም መካሄዳቸውን ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡