የሀገር ውስጥ ዜና

800 ሚሊየን ብር የሚገመቱ የህክምና ግብዓቶች ለ5 ሆስፒታሎች ተበረከተ

By Meseret Awoke

December 13, 2024

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት 800 ሚሊየን ብር የሚገመቱ የመድሀኒት እና የህክምና ግብዓቶች ለአምስት የመንግስት ሆስፒታሎች አበርክቷል።

መድሀኒቶቹንና እና የህክምና ግብዓቶቹን ለሆስፒታሎቹ ያስረከቡት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ ናቸው።

በርክክቡ ወቅትም÷ የተደረገው ድጋፍ ሆስፒታሎችን በብዙ መልኩ እንደሚረዳ የጠቆሙት የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት “ሁላችንም የአቅማችንን በማድረግ አጋጣሚዎችን ተጠቅመን ለኢትዮጵያ በጋራ ከሰራን ለውጥ እናመጣለን “ብለዋል።

የመድሃኒትና የህክምና ግብዓቶቹ ከሙስሊም ኤድ አሜሪካ በኡስታዝ አቡበከር አህመድ አስተባባሪነት የተገኙ መሆናቸውም ተገልጿል።

ድጋፉ የተደረገውም ለድልጮራ ሆስፒታል፣ ለአሶሳ ሆስፒታል፣ ለጅግጅጋ ሆስፓታል፣ ለሙሁር አክሊል የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል፣ ለስልጤ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ነው፡፡

ከዚህ በፊት ሥድስት ጊዜ የመድሃኒት እጥረት ላለባቸው አካባቢዎች በተመሳሳይ ድጋፍ መደረጉ ተመላክቷል።

በፈቲያ አብደላ