የሀገር ውስጥ ዜና

 ኢትዮጵያና ኡጋንዳ ከስደተኞች ጋር በመመሸግ ወንጀል የሚፈጽሙትን በጋራ ለመከላከል መግባባት ላይ ደረሱ

By Mikias Ayele

December 14, 2024

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ኡጋንዳ ከስደተኞች ጋር መሽገው ወንጀል የሚፈፅሙትን በጋራ ለመከላከልና ለመስራት መግባባት ላይ ደረሱ።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከኡጋንዳ ኢታማዦር ሹም ጄነራል ሙሆዚ ካኒሩግባ ከተመራ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል።

ኡጋንዳና ኢትዮጵያ ዘመናትን የተሻገረ የሁለትዮሽ ግንኙነት እና ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን የገለፁት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ በዛሬው ዕለት የቀደሙ ትስስሮችን የሚያጠናክሩ ውይይቶችን አድርገናል ብለዋል።

በተለይ በሁለቱ ሀገራት በስደተኞች ሰበብ መሽገው የወንጀል ድርጊት የሚፈጽሙ ወንጀለኞችን ለመከላከል በጋራ ለመስራት ተወያይተናል ብለዋል።

በዚህም ሁለቱ ሀገራት የፀጥታ መረጃ መቀያየር፣ ሁሉን አቀፍ ስልጠና እንዲሁም ለቀጣናው ሰላም በጋራ ለመስራት የሚያስችል ውይይት አድርገዋል።

ጄነራል ሙሆዚ ካኒሩግባ በበኩላቸው በሰላምና ፀጥታ ዘርፍ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር የተጠናከረ ግንኙነት እንዳላት ገልጸው፤ በቀጣይ የሀገራቱን ሁሉን አቀፍ ትብብር ለማጠናከር በቁርጠኝነት እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

በሳሙኤል ወርቃየሁ