አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ አመራሮች በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚያደርጉት የልማት ሥራዎች ምልከታ እንደቀጠለ ነው።
በዚሁ መሠረት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ባደረጉት ጉብኝት አካባቢው መደበኛ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።
ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ በነበረን የመስክ ጉብኝት የተመለከትነው እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ ነው ብለዋል።
በህዝቡ ባለቤትነትና ተሳትፎ፣ በአመራሩ ቁርጠኝነትና አስተባባሪነት፣ በፀጥታ ኃይሉ መስዋዕትነትና ጀግንነት አካባቢው በአሁን ሰዓት በእጅጉ ወደተሻለ የሰላም ግንባታ እና የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ ገብቷል ሲሉ ገልጸዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ከተማ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በመከናወን ላይ የሚገኙ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል፡፡
እንዲሁም የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በአማራ ክልል እያደረጉት ያለውን ጉብኝት በመቀጠል ዛሬ በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን አርጡማ ፉርሲ ወረዳ ብሼ ኤዴዳ ቀበሌ የበጋ ስንዴ ዘርን አስጀምረዋል።
በተመሳሳይ በድሬዳዋ አሥተዳደር ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት የማዕድን ሚኒስትር ሀብታሙ ተገኝ (ኢ/ር) በአሥተዳደሩ የኢንዱስትሪዎችን የሥራ እንቅስቃሴ ጨምሮ በከተማ ግብርና የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን ተመልክተዋል።
በሌላ በኩል የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በጋምቤላ ክልል ዲማ ወረዳ እየተከናወነ ያለውን የወርቅ ማዕድን ሀብት ልማት መጎብኘታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡
የኢንዱስትሩ ሚኒስትር መላኩ አለበልም በጎንደር ከተማ እየተከናወኑ ያለ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል፡፡
በጉብኝቶቹ ከሚኒስትሮቹ በተጨማሪ የየክልሎቹ እና ከተማ አሥተዳደሮቹ አመራሮችም ተካትተዋል፡፡