የሀገር ውስጥ ዜና

የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተለያዩ አካባቢዎች የመስክ ምልከታ እያካሄዱ ነው

By Feven Bishaw

December 17, 2024

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመስክ ምልከታ እያደረጉ ነው።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በሸካ ዞን አንድራቻ ወረዳ ተገኝተው የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።

በጉብኝታቸውም በወረዳዉ ዮኪጭጭ ቀበሌ በሴቶች አደረጃጀት እየተከናወኑ የሚገኙ የማር መንደርን እና የሞዴል አርሶአደር ገቢቶ ሾደኖ 4 ሄክታር የእንሰት ማሳን ተመልክተዋል።

በዞኑ የተሰሩ የልማት ተግባራት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ተሞክሮው ሊስፋፋ እንደሚገባ ገልጸው፤ ዞኑ የሌማት ትሩፋትን ምንነት በተገቢው ተረድቶ በተግባር ያሳየ አካባቢ መሆኑን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ(ዶ/ር) እና በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር ) የተመራ ቡድን በአዲስ አበባ ከተማ በአራዳ ክፍለ ከተማ የተገነባውን የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት ተዘዋውሮ ጎብኝቷል።

ግንባታው ሲጠናቀቅ የወንዙን ሕልውና በመታደግና የከተማዋን ገጽታ በመቀየር ነፋሻማና ለመኖሪያ ምቹ አካባቢን እንደሚፈጥር አስረድተዋል።

በተጨማሪም አራት ኪሎ ፕላዛ የውስጥ ለውስጥ የእግረኛ መንገድና ከአራት ኪሎ ፒያሳ መሀል የሚገኘው የራስ መኮንን የመስታወት ድልድይ ግንባታ ከተማዋን የሚመጥን በመሆኑ ለገጽታ ግንባታ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው መገለጹን የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመለክታል።

በጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ የተመራ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች  የልዑካን ቡድን በኮንሶ ዞን የልማት ስራዎችን ጎብኝቷል፡፡

 

በጉብኝቱ  የኮሪደር ልማት እንቅስቃሴዎችን፣ የሌማት ትሩፋት ስራዎችን፣የካራት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልን  እንዲሁም ባህላዊ ቅርሶችን ተመልክተዋል፡፡

 

በዞኑ በነበረው የመስክ ምልከታ አበረታች ነገሮችን መመልከታቸውን የተናገሩ ሲሆን÷በተለይ በግብርናው ዘርፍ ያሉ የሌማት ትሩፋት ስራዎች የሚበረታቱና ሊቀጥሉ የሚገባቸው መሆናቸው ተገልጿል፡፡

በተመሳሳይ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)የተመራው የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች ቡድን በማጃንግ ዞን በጎደሬና በመንገሺ ወረዳዎች የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎብኝቷል።

በሚኒስትሯ የተመራው ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ቡድን ከጎበኛቸው የልማት ስራዎች መካከል የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት፣ በሙከራ ደረጃ ላይ ያለ የስንዴ ልማትና በውጭ ሀገር ባለሃብት እየለማ ያለ የሻይ ቅጠል ልማት ይገኝበታል።

ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት÷ በዞኑ በገቢ ማስገኛ የግብርና ልማት ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ተመልክተናል ብለዋል።

ክልሉ ለግብርናው ልማት አመቺ የሆነ የተፈጥሮ ሃብት ያለበት አካባቢ በመሆኑ ይህንን ሀብት እሴት ጨምሮ ለማልማትና የህዝቡን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ የተጀመሩ ጥረቶች ሊጠናከሩ እንደሚገባም ሚኒስትሯ አስገንዝበዋል።