አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በጥራጥሬና ቅባት እህሎች ምርት አቅርቦት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነቷን እያሳደገችና በዘርፉ ያላትን ገጽታ እየገነባች መምጣቷን የኢትዮጵያ ቅባትና ጥራጥሬ እህሎች ማህበር ገለጸ፡፡
በጥራጥሬና የቅባት እህሎች ኢንቨስትመንት ዙሪያ ባተኮረ ምክክር የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ያስሚን ወሐብረቢን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ላኪዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታ ያስሚን ወሐብረቢ በዚሁ ወቅት ፥ መንግስት ለግብርናው ዘርፍ የሰጠው ትኩረት ከፍተኛ ውጤት እንዲመዘገብ ማስቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
ግብርናን ለማሳለጥ የሚረዱ አስቻይ ፖሊሲዎችን በመቅረጽ ተግባራዊ መደረጉ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችንና ማነቆዎች መፍታት ማስቻሉን አስረድተዋል፡፡
ይህም ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያድግ አድርጎታል ብለዋል፡፡
በግብርናው ዘርፍ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ረገድ የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ድርሻ በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉንም አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ስርዓት ውስጥ ለመግባትና የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና ተዋናይ ለመሆን እየተዘጋጀች መሆኗንም ተናግረዋል፡፡
ሂደቱ ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ያላትን የንግድ እንቅስቃሴ ከፍ እንደሚያደርገው ገልጸው ፥ በተለይም በግብርና ወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ላኪዎች ምርቶች ላይ እሴት መጨመር ላይ በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ቅባትና ጥራጥሬ እህሎች ማህበር ስራ አስኪያጅ ኤዳኦ አብዲ በበኩላቸው ፥ ኢትዮጵያ በጥራጥሬና የቅባት እህል ምርትን ለውጪ ገበያ በማቅረብ በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እየሆነችና በዘርፉ ያላትን ገጽታ እየገነባች መምጣቷን ጠቅሰዋል፡፡
ማህበሩ ከመንግስት ጋር ተቀራርቦ መስራቱ ለተገኘው ውጤት ወሳኝ ሚና መጫወቱን በማንሳት በቀጣይም በመንግስት የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡