የሀገር ውስጥ ዜና

ፕሬዚዳንት ማክሮን ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ

By Meseret Awoke

December 21, 2024

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በሥድስት ዓመታት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ለይፋዊ ሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ፡፡

ፕሬዚዳንቱ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ ወንድሜና የኢትዮጵያ የልብ ወዳጅ የፈረንሳይ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ባለፉት ስድስት ዓመታት ለሁለተኛ ጊዜ ለጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ እንኳን ደህና መጡ ብለዋል፡፡

በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት የበለጠ በመጠናከር ላይ እንደሚገኝም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) አስገንዝበዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ፍሬያማ ውይይት እንደሚኖረን እምነቴ ፅኑ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡