አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ መካከል ያሉ ዘርፈ-ብዙ ትብብሮችን በይበልጥ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከፕሬዚዳንት ማክሮን ጋር መምከራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ከፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር በብሔራዊ ቤተ-መንግሥት የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡
በውይይታቸውም ሰፋ ያለ መጠነ-ርዕይ ባላቸው የሁለትዮሽ እና ባለብዙ ወገን ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ነው የገለጹት፡፡
ፕሬዚዳንቱ እና የፈረንሳይ መንግሥት ለብሔራዊ ቤተ መንግስት እና በመካሄድ ላይ ባለው የላሊበላ ውቅር አብያተ-ክርስቲያናት እድሳት ሥራዎች ላደረጉት አስተዋፅዖም ምሥጋና አቅርበዋል፡፡
በውይይታችን በተለያዩ ዘርፎች የሚኖሩ ትብብሮችን ፈትሸናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ ለአብነትም የፈረንሳይን ኢንቨስትመንት መጨመር ብሎም በትምህርት እና ባሕል ዘርፎች ያለንን ግንኙነት ለማጠናከር ባለሙ ጉዳዮች ላይ ተነጋግረናል ነው ያሉት።
በተጨማሪም ታሪካዊ ትስስራችንን በይበልጥ የመገንባት አስፈላጊነትን በውይይታችን አፅንዖት ሰጥቼ አንስቻለሁ ብለዋል።