የሀገር ውስጥ ዜና

ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል ያለመ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ ተጀመረ

By Feven Bishaw

December 24, 2024

 

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል ያለመ ሀገር አቀፍ የንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ዛሬ በድሬዳዋ ተካሂዷል።

መርሐግብሩ ማህበራዊ እሴቶችን ለማጎልበትና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል የሚያግዝ መሆኑ እንዲሁም ወጣቶችን ከመጤ ባህል ወረርሽኝ ለመጠበቅና በዘርፉ በቂ ግንዛቤ ለመፍጠር ለማስቻል ያለመ ነው ተብሏል።

በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችና በእግር ጉዞ መርሐግብሩን ያስጀመሩት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ በወቅቱ እንደተናገሩት÷ ብዝሃ ማንነቶቻችንና ዘመን ተሻጋሪ እሴቶቻችንን በመጠበቅና በማጎልበት ለሀገር እድገትና የብልጽግና ጉዞ ማሳኪያ እንዲውሉ በትኩረት እየተሰራ ነው።

ጠቃሚ እሴቶቹን ከትውልድ ወደ ትውልድ በማሸጋገር ወጣቶችን ተጠቃሚ በማድረግና ለሀገር ግንባታ እንዲውሉ ስትራቴጂ ተነድፎ እየተሰራ መሆኑን ለአብነት በማውሳት።

የድሬዳዋ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሚካኤል እንዳለ በበኩላቸው÷ በአስተዳደሩ ወጣቶች ጊዜያቸውን በስፖርትና በንባብ እንዲያሳልፉ የተቀናጀ ስራ እየተሰራ መሆኑን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ሀገርአቀፍ የንቅናቄ መርሐግብሩ በሁሉም ክልሎችና ከተሞች የሚካሄድ መሆኑ ተመላክቷል።