አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል በረሃማ አካባቢዎች ያለውን የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ለማሻሻል የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም የሚችሉ ፕሮጀክቶች እየተተገበሩ መሆኑ ተገለጸ፡፡
በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዞን እየተተገበሩ ካሉ የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች መካከል ግንባታቸው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኙት የጨፋ ሮቢት ከተማና የከሚሴ ከተማ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች ተጎብኝተዋል፡፡
የአማራ ክልል ውኃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ማማሩ አያሌው (ዶ/ር) እንደገለጹት÷ በተያዘው በጀት ዓመት በዘርፉ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ሕዝቡ የንጹህ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሠራ ነው፡፡
የጨፋሮቢት እና ከሚሴ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች አፈጻጸምም አበረታች መሆኑን ገልጸው÷ በአጭር ጊዜ ተጠናቅቀው አገልግሎት እንደሚሰጡ አረጋግጠዋል፡፡
ቢሮው ከውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በዞኑ በርሃማ አካባቢዎች ያለውን የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ለማሻሻል የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም የሚችሉ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየተገበረ ነው ብለዋል፡፡
የብሔረሰብ ዞን አሥተዳደሩ ዋና አሥተዳዳሪ አሕመድ ዓሊ በበኩላቸው የክልሉ መንግሥት የብሔረሰብ አሥተዳደሩን ማሕበረሰብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እያደረገ ላለው ትጋት አመሥግነው÷ ጥረቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ጠይቀዋል፡፡