የሀገር ውስጥ ዜና

ግድቦች ለማመንጨት የታቀደውን ሃይል ማሳካት የሚያስችል ውሃ መያዛቸው ተገለጸ

By Melaku Gedif

December 26, 2024

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፈው የክረምት ወቅት ወደ ኃይል ማመንጫ ግድቦች የገባው የውሃ መጠን በበጀት ዓመቱ ለማመንጨት የታቀደውን ዕቅድ ለማሳካት እንደሚያስችል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታውቋል፡

በተቋሙ የኃይል ማመንጫዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ የዕቅድ ቢሮ ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ጥሩወርቅ ሽፈራው እንደገለጹት÷ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች በሙሉ አቅማቸው ኃይል እንዲያመነጩ ለማድረግ ግድቦች በቂ ውሃ መያዝ ይኖርባቸዋል፡፡

በክረምቱ ወቅት ከፍተኛ የውሃ መጠን ያከማቹ ማመንጫ ጣቢያዎች ከፍተኛ ኃይል እንዲያመነጩ በማድረግ አነስተኛ ውሃ የነበራቸው ግድቦችን የኃይል ጭነት በመቀነስ በተገቢው መጠን ውሃ እንዲይዙ መደረጉን ተናግረዋል።

በአሁኑ ጊዜ ግድቦቹ የያዙት የውሃ መጠን በበጀት ዓመቱ ለማመንጨት የታቀደውን ለማሳካት እንደሚያስችል በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የነበረው ኃይል የማመንጨት አፈፃጸም ማሳያ ነው ብለዋል።

እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በተሰበሰበው መረጃ መሰረት ስምንት የማመንጫ ግድቦች የሞሉ ሲሆን÷ ሁለቱ ደግሞ በበቂ ደረጃ ውሃ መያዛቸውን ነው ሥራ አስኪያጇ የጠቆሙት።

ግልገል ጊቤ 1ኛ፣ ፊንጫ፣ መልካ ዋከና፣ ጣና በለስ፣ ተከዜ፣ ገናሌ ዳዋ፣ ቆቃ እና ህዳሴ የኃይል ማመንጫ ግድቦች የሞሉ ሲሆን÷ ጊቤ 3ኛ እና አመርቲ ነሼ ኃይል ማመንጫ ግድቦች ደግሞ በበቂ ደረጃ ውሃ ይዘዋል ነው ያሉት፡፡

ሁሉም ግድቦች አሁን ያላቸው የውሃ መጠን በበጀት ዓመቱ የታቀደላቸውን ኢነርጂ ለማመንጫት እንደሚያስችላቸውም አረጋግጠዋል፡፡

ግድቦች የያዙትን የውሃ መጠን በአግባቡ ለመጠቀም ከጥገና፣ ከውሃ አስተዳደር እና ከመለዋወጫ ዕቃዎች አቅርቦት ጋር በተያያዘ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

የ2017 በጀት ዓመት የግድቦች የውሃ አያያዝ ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጸር የተሻለ እንደሆነ በዳሰሳ ጥናት መረጋገጡን አንስተዋል፡፡

በተያዘው የበጀት ዓመት ከተለያዩ የኃይል ምንጮች ከ25 ሺህ ጊጋ ዋት ሰዓት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማምረት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የተቋሙ መረጃ ያመላክታል፡፡