የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ ለምሥራቅ አፍሪካ ሰላምና ደኀንነት መጠበቅ ያላትን ሚና እንደምታጠናክር ገለጸች

By Meseret Awoke

December 26, 2024

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ለምሥራቅ አፍሪካ ሰላም እና ደኀንነት መጠበቅ ያላትን ሚና አጠናክራ ትቀጥላለች ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አዘጋጅነት በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ለነባር ዲፕሎማቶችና ለወጣት በጎ ፈቃደኛ ካዴቶች ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡

በዚህ ወቅት አምባሳደሩ÷ ኢትዮጵያ የቀጣናው አስተማማኝ ሰላምና ደኀንነት እንዲጠበቅ እንዲሁም የተረጋጋ እንዲሆን ከሌሎች ሀገራት ጋር ጉርብትናን በማጠናከር በትብብር እንደምትሰራ ገልጸዋል።

ተለዋዋጭ በሆነው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በመርህ ላይ በመመስረት በኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ግንኙነት መስኮች እንዲጠናከሩ በጋራ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም በተሟላ ሁኔታ ለማስከበርና የሕዝብን አደራ ለመወጣት በመጪው የካቲት ወር አጋማሽ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኀብረት የመሪዎች ጉባኤ እንደሚካሄድ አውስተዋል፡፡

በዚህም ጉባኤውን በተሳካ ሁኔታ ለማስተናገድ ዲፕሎማቶችና ወጣት በጎ ፈቃደኛ ካዴቶች በሀገራዊ ፍቅር ስሜት ሊሰሩ ይገባል ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡