የሀገር ውስጥ ዜና

በትግራይ ክልል ከ640 ሺህ በላይ ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት እየተከናወነ ነው

By yeshambel Mihert

December 28, 2024

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በትግራይ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት ከ640 ሺህ በላይ ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርግ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የውሃና ኢነርጂ ቢሮ ገለፀ።

በቢሮው የመጠጥ ውሀ አቅርቦት ዳይሬክተር አቶ ታጠረ ሐዱሽ÷በክልሉ ያለውን የንፁህ መጠጥ ውሀ እጥረት ለማቃለል መንግስት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

በክልሉ 32 በመቶ የነበረው የንፁህ መጠጥ ውሀ ሽፋን በበጀት ዓመቱ ወደ 40 በመቶ ከፍ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከሥራዎቹ መካከል የ50 መካከለኛና የአምስት ጥልቅ ጉድጓዶች ቁፋሮ፣ የስምንት መካከለኛ ጉድጓዶች የውሃ መስመር ዝርጋታ ይገኙባቸዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በአሁኑ ወቅት እየተከናወኑ ያሉት ስራዎች በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ሲጠናቀቁ 649 ሺህ ህዝብን የንፁህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ ያደርጋልም ተብሏል፡፡