አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሐረሪ ክልል ከደረጃ በታች የሆኑ ስድስት የግል ኮሌጆች መዘጋታቸውን የክልሉ ቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና ኤጀንሲ አስታወቀ።
የኤጀንሲው ኃላፊ ወ/ሮ ነቢላ ማህዲ ÷ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ በተደረገ ክትትል እና ግምገማ ከደረጃ በታች ሆነው የተገኙ ስድስት ኮሌጆች እንዲዘጉ መደረጉን ገልጸዋል።
ኮሌጆቹ በአግባቡ ያልተደራጁ፣ ምቹ የትምህርት አካባቢ የሌላቸው፣ በተበታተኑ ማዕከላት ሲያስተምሩ የነበሩ እና የትምህርት ጥራት ችግር የተስተዋለባቸው መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ ለተግባር ትምህርት አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን ያላሟሉ፣ የአገልግሎት ዘመናቸው ባለፈ መድሃኒቶች የሚገለገሉ እና ባልተመዘኑ መምህራን ሲያስተምሩ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡
የማስተማሪያ እውቅናቸውን ሳያድሱ ጊዜው ባለፈበት ፈቃድ ሲጠቀሙ የነበሩ እና ገበያው ላይ ተፈላጊነት ያላቸው ትምህርቶች ላይ ትኩረት ያላደረጉ ናቸውም ብለዋል።
በዚህ መሰረትም አፍራንቀሎ፣ ሪፍት ቫሊ፣ አዋሽ ቫሊ፣ ወሊፍ፣ ሉሲ እና ሙርቲ ጉቱ ኮሌጆች በክልሉ ከደረጃ በታች ሆነው በመገኘታቸው መዘጋታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡