አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግሥት የሀገርን መሰረታዊ ጥቅም የሚጎዱ ሕገ-ወጥ የንግድ ተግባራትን ለመቆጣጠር በአሠራርና በፖሊሲ የተደገፈ ሥራ እያከናወነ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።
3ኛው ሀገር አቀፍ የሕገ-ወጥ ንግድ መከላከል ጉባዔ በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አዘጋጅነት ዛሬ ተካሂዷል፡፡
ሚኒስትሩ በጉባዔው ላይ ባደረጉት ንግግር÷ መንግሥት የሀገርን መሰረታዊ ጥቅም የሚጎዱ ሕገ-ወጥ የንግድ ተግባራትን ለመቆጣጠር እየሰራ ነው ብለዋል።
ሕጋዊ ነጋዴዎች የመኖራቸውን ያህል በሕገ-ወጥ ንግድ ላይ የተሰማሩ አካላት መኖራቸውን አስገንዝበው፤ እነዚህ በሕገ-ወጥ ንግድ ላይ የተሰማሩ አካላት የሀገር ጠንቅ በመሆናቸው በጋራ ልንታገላቸው ይገባል ሲሉ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ያለ ንግድ ፈቃድ መነገድ፣ ከተፈቀደ መጠንና ኮታ በላይ ምርትን ማዘዋወር፣ እጥረትን ለመፍጠር ምርትን አከማችቶ መያዝ፣ ያለበቂ ምክንያት በምርቶች ላይ ዋጋ ጨምሮ መሸጥና መሰል ተግባራት ሕገ-ወጥ ንግድ መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡
መንግሥት ሙሉ አቅሙን ቁጥጥርና ክትትል ላይ እንዲያውል የግሉ ዘርፍ ራሱን ከሕገ-ወጥ ንግድ እንቅስቃሴ ነጻ ሊደርግ ይገባል ብለዋል፡፡