አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ለመጪው የገና እና ሌሎች በዓላት ከውጪ የተገዛ 34 ሚሊየን ሊትር የፓልም ዘይት ወደ ሀገር ውስጥ መግባት ጀምሯል።
ዘይቱ የመንግስት ልማት ድርጅት በሆኑት በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት (ኢግልድ) እና በንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የተገዛ ነው ተብሏል።
በዛሬው ዕለትም የተገዛው የፓልም ዘይት በባቡር ተጓጉዞ በአዲሰ አበባ መራገፍ ጀምሯል።
የኢግልድ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ የሺእመቤት ነጋሽ እንዳሉት፥ የተለያዩ መሠረታዊ የፍጆታ እቃዎች አቅርቦት ለማሳለጥ በትኩረት እየተሰራ ነው።
ዛሬ ወደ ሀገር መግባት የጀመረው ዘይትም በበዓል ሰሞን የሚስተዋለውን የዋጋ ጭማሪ ለማረጋጋት ያስችላል ብለዋል።
የመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎችን ዋጋ ለማረጋጋት ኢግልድ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት።
በመላኩ ገድፍ