አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዕቅድ፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት መቋቋም ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አድገት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ገለጸ።
ቋሚ ኮሚቴው የኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩትን ለማቋቋም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ የአስረጂዎች መድረክ አካሂዷል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዳሳለኝ ወዳጆ፣ ረቂቅ አዋጁ ጠንካራና ተፈጻሚ ሆኖ እንዲጸድቅ መሰረታዊ ሀሳቦች ሊካተቱ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በሌላ በኩል ቋሚ ኮሚቴው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እያሉ የኢንስቲትዩቱ መቋቋም ለምን አስፈለገ የሚለውን ጨምሮ በአዋጁን ጠቀሜታ ዙሪያ ዝርዝር ጥያቄዎችን አንስቷል።
የሂሳብ አያያዝ ኦዲት ቦርድ ምክትል ዳይሬክተር ፅዋዬ ሙሉነህ፣ ኢንስቲትዩቱ መቋቋም ያስፈለገበት ምክንያት ብቁ የሂሳብ ባለሙያዎችን በማፍራት ነጻና ገለልተኛ ሆነው መስራት እንዲችሉ ነው ብለዋል።
የኢንስቲትዩቱ መቋቋም ብቁና ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪ የሂሳብ ባለሙያዎችን ለማፍራት እንደሚያግዝ እና በዘርፉ የሚታየውን የሙያተኛ እጥረት ለመቅረፍ እንደሚያስችልም ተናግርዋል።
በረቂቅ አዋጁ ትርጉምን ጨምሮ መካተት ያለባቸው መሰረታዊ ሀሳቦች ሊካተቱ እንደሚገባም መገለጹን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡