የሀገር ውስጥ ዜና

የሕዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ – አቶ አረጋ ከበደ

By Melaku Gedif

January 03, 2025

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላም በማስፈን የሕዝቡን የልማት ተጠቃሚነት የሚያረጋገጡ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።

የብልጽግና ፓርቲን መርሆዎችና እሴቶች አጠናክሮ ለማስቀጠል “ከቃል እስከ ባህል” በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀ የብልጽግና ፓርቲ 2ኛው የቅድመ መደበኛ ጉባኤ ኮንፈረንስ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ርዕሰ መስተዳድሩ ባደረጉት ንግግር፤ ፓርቲው ከተመሰረተ ጀምሮ ያጋጠሙ ችግሮችን በማለፍ የተገኙ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ድሎችን እንደሚመለከት ተናግረዋል።

ኮንፈረንሱ ፖለቲካዊ እሳቤዎችን የምናጠናክርበት፣ የልማትና መልካም አስተዳደር ስራ አፈጻጸማችንን በመገምገም ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የምንተጋበት በመሆኑ በንቃት መሳተፍ ይገባናል ብለዋል።

የአመራር አባላትን የአስተሳሰብና የአመለካከት አንድነት በማጎልበት አባላትና ደጋፊዎች ለላቀ ተልዕኮ የሚዘጋጁበት መሆኑን አስረድተዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ የጽህፈት ቤት ሃላፊ ይርጋ ሲሳይ በበኩላቸው፤ ፓርቲው ባለፉት ዓመታት በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስኮች አመርቂ ስኬቶች ማስመዘግቡን ገልጸዋል።

በህብረ ብሄራዊ አንድነት መርህ በየደረጃው የዴሞክራሲያዊ አንድነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ በኩልም ለውጥ ማምጣት መቻሉን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።