የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ ለከተራና የጥምቀት በዓል በታቦታት ማደሪያ ቦታዎች የጽዳት መርሐ ግብር እየተከናወነ ነው

By Feven Bishaw

January 17, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ለከተራና የጥምቀት በዓል በሁሉም የታቦታት ማደሪያ ቦታዎች “የጥምቀት በዓል በፅዱ አዲስ አበባ” በሚል መሪ ሀሳብ የጽዳት መርሐ ግብር እየተከናወነ ነው።

የከተማዋ ዋና ስራ አስኪያጅ ወንድሙ ሴታ (ኢ/ር)፤ የጥምቀትና የከተራ በዓልን ምክንያት በማድረግ በሁሉም የታቦት ማደሪያ ቦታዎች የማጽዳትና ምቹ የማድረግ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

በዓሉን ለማክበር ወደ ከተራና ጥምቀት ለሚጓዙ እግረኞችና ለተሽከርካሪዎች መንገዶችን የማስተካከል ሥራዎች መከናወናቸውን አንስተው፤ አዲስ አበባን ውብና ፅዱ የማድረግ ሥራ ትኩረት እንደተሰጠውም ነው የገለጹት።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የፕሮጀክት መምሪያ ኃላፊ መልአከ ሕይወት ቆሞስ አባ ወልደኢየሱስ ሰይፉ፥ የጥምቀት በዓል ፍቅርንና አብሮነትን የሚያስተምር ነው ብለዋል።

የጥምቀት በዓል የሚከበርበትን ስፍራ በአብሮነት በማጽዳት የተባበሩትን የሁሉንም ሃይማኖት ተወካዮችና የህብረተሰብ ክፍሎች አመስግነዋል።

የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ፀሐፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ፥ ሃይማኖታዊ በዓላት ሁሉም ህብረተሰብ አንድነቱንና ትብብሩን የሚያጠናክርባቸው መልካም እሴቶቻችን ናቸው ብለዋል።

ይህም በዓላቱ ደምቀውና አምረው እንዲከበሩ በማድረግ የሀገር ገፅታ እየገነባ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በመርሐ ግብሩ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች፥ የሁሉም ሃይማኖቶች ተወካዮች፣ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።