የሀገር ውስጥ ዜና

ከ730 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ደንበኞች የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር አገልገሎት ተሰጥቷል

By Mikias Ayele

January 17, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ስድስት ወራት ከ730 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ደንበኞች አገልገሎት መስጠት መቻሉን የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ገለፀ፡፡

ባለስልጣኑ የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያዉ ግማሽ ዓመት እቅድ አፈፃፀሙን ገምግሟል።

በግምገማ መድረኩ ባለስልጣኑ ባለፉት ስድስት ወራት የአሽከርካሪዎች ስልጠና ምዝገባ፣የብቃት ማረጋገጫ፣የአሽከርካሪዎች የመንጃ ፈቃድ እድሳት አገልግሎት እና የውጭ መንጃ ፈቃድ ቅያሬ አገልግሎቶችን ሲሰጥ መቆየቱ ተገልጿል፡፡

እንዲሁም አዲስ መኪና ምዝገባ፣የተሸከርካሪዎች ዓመታዊ ብቃት ማረጋገጫ(ቦሎ)፣የስም ዝውውር እና ድንገተኛ ምርመራ አገልግሎቶችም በባለስልጣኑ በግማሽ አመት ውስጥ የተከናወኑ ተግባራት ናቸው፡፡

በዚህም በአጠቃላይ በአሽከርካሪ እና በተሽከርካሪ ዘርፍ  ለ733 ሺህ 541 ተገልጋዮች አገልግሎት መስጠጡን እና ከተሰጠዉ አገልግሎት ከ2 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱ ተመላክቷል፡፡

በመድረኩ የባለስልጣኑ አመራሮች፣ሰራተኞች እና ባለድርሻ አካላት የተቋሙን አገልግሎት በማዘመን የተመዘገቡ ውጤቶችን እንዲያስቀጥሉ መመሪያ መሰጠቱን የባለስልጣኑ መረጃ ያመላክታል፡፡