አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2016/17 የምርት ዘመን 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል የጥጥ ምርት መሰብሰቡን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በግብርና ሚኒስቴር የጥጥ ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ሳምሶን አሰፋ እንደገለጹት÷ ለጥጥ ልማት እንደ ገዋኔ፣ መተማ፣ ሑመራ፣ ጋሞ፣ ጎፋ ወላይታና ደቡብ ኦሞ ያሉ ቆላማ የአየር ንብረት ያላቸው አካባቢዎች ተመራጭ ናቸው፡፡
በተጨማሪም በጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች እንዲሁ ሰፋፊ የጥጥ እርሻዎች እንደሚለሙ አክለዋል።
በሀገሪቱ በ2016/17 የምርት ዘመን በ107 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ጥጥ የማልማት ስራ መከናወኑንም ገልጸው፤ ከዚህ ውስጥ 6 ሺህ ሄክታሩ በመስኖ የለማ መሆኑን ገልጸዋል።
ከተሰበሰበው 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል ጥሬ ጥጥ ውስጥ 65 ሺህ ሜትሪክ ቶን የሚሆነውን በመዳመጥ ለገበያ ዝግጁ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።
ዘንድሮ የተገኘው የጥጥ ምርት ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ5 ሺህ ሜትሪክ ቶን ብልጫ ማሳየቱን ጠቁመዋል።
ምርቱን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ አስፈላጊው ዝግጀት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት በቻይናና ህንድ ያሉ የጨርቃጨርቅ አምራቾች የጥጥ ምርት ጥያቄ ማቅረባቸውንም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ለጥጥ ልማት ተስማሚ ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ በመሆኗ ምርቱን ለማሳደግ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በአሁኑ ወቅት የጥጥ ምርት በሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች ላይ አገልገሎት እየሰጡ ያሉ 20 የጥጥ መዳመጫ ፋብሪካዎች መኖራቸውንና ተጨማሪ 10 ፋብሪካዎችን ወደ ስራ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም አቶ ሳምሶን ጠቁመዋል።