የሀገር ውስጥ ዜና

ከተራና ጥምቀትን ስናከብር ትስስራችንን በሚያጠናክር ተግባር መሆን አለበት- ምክር ቤቱ

By Feven Bishaw

January 18, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የከተራና እና ጥምቀት በዓላትን ስናከብር ማህበራዊ ትስስራችንንና አብሮነታችንን በሚያጠናክሩ ተግባራትን ሊሆን ይገባል ሲል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስገነዘበ፡፡

ምክር ቤቱ ለከተራ እና ጥምቀት በዓላት የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላልፏል፡፡

በመልዕክቱም የጥምቀት በዓልን ስናከብር ከሐይማኖታዊ በዓልነቱ ባለፋ ለማህበራዊ ኢኮኖሚ ልማት የሚያስገኘውን አበርክቶ በመገንዘብና ይህንኑ በማጠናከር ሊሆን ይገባል ብሏል፡፡

የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሣችሁ! አደረሰን!

የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለከተራና ጥምቀት በዓል አደረሳችሁ ሲል የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፏል።

የጥምቀት በዓል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው በየዓመቱ በደማቅ አከባበር የሚከበር የአደባባይ በዓል ነው።

ሀገራችን በዩኔስኮ በቅርስነት ካስመዘገበቻቸው ከማይዳሰሱ ብሔራዊ ቅርሶች መካከል አንዱ የሆነው የጥምቀት በዓል ሐይማኖታዊ ሥርዓቱንና ትውፊቱን ጠብቆ መከበር ከጀመረ ረጅም ዘመናትን አስቆጥሯል።

ሕዝበ ክርስቲያን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በተለያዩ አልባሳትና ጌጣጌጦች አጊጠው ፣ አሸብርቀውና ደምቀው የተለያዩ ሐይማኖታዊ ሥርዓቶችን በመፈፀም ታቦታቱን በዕልልታና ጭብጨባ እያጀቡ የከተራና የጥምቀት በዓልን በደስታና በፍቅር ያሳልፉታል።

በዓሉ ከሐይማኖታዊ አምልኮተ ሥርዓቱ ባለፈ ለማህበራዊ ትስስርና ለአብሮነታችን መጠናከር ፣ ለገፅታ ግንባታና ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ዕድገት ያለው አበርክቶ እጅግ ከፍተኛ ነው።

ስለሆነም የጥምቀት በዓልን ስናከብር ከሐይማኖታዊ በዓልነቱ ባለፋ ለማህበራዊ ኢኮኖሚ ልማት የሚያስገኘውን አበርክቶ በመገንዘብና ይህንኑ በማጠናከር ሊሆን ይገባል።

የጥምቀት በዓል ፍቅር ሠላምና ትህትና የተገለጠበት እንደ መሆኑ የከተራና የጥምቀት በዓልን ስናከበር ኃይማኖታዊ አስተምህሮውን በጠበቀ፣ ማህበራዊ ትስስራችንንና አብሮነታችንን በሚያጠናክሩ ተግባራትን በማከናወን ፣ በፍቅር ፣ በሠላም፣ ለተቸገሩ ወገኖች ካለን በማካፈል፣ በመተሳሰብ ስሜትና ተግባራት ሊሆን ይገባል።

እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሣችሁ ! አደረሰን!