አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፍሪካ ቀንድ የንግድና ሎጂስቲክስ ስርዓቱን ለማሻሻልና ለመለወጥ የሚያስችል የንግድ ማበልፀጊያ ኮንፍረንስ መካሄድ ጀምሯል።
በኢትዮ ሎጂስቲክስ ዘርፍ ማህበራት የተዘጋጀው ኮንፍረንሱ በኢትዮጵያ፣ ጅቡቲና በሌሎች የአካባቢው ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ ለማሳደግ የሚያስችል ምክክር ለማካሄድ እንደሚያግዝ ተገልጿል።
የጋራ እድገትን ለማምጣት ብሎም ንግድና ሎጂስቲክስን ለማሳለጥም ሚናው የጎላ ስለመሆኑ ተመላክቷል።
በመድረኩ የኢትዮ ሎጂስቲክስ ዘርፍ ማህበራት ፕሬዚዳንት ኤልሳቤጥ ጌታሁን÷ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለመደገፍና ቀጣናዊ ጥያቄዎች ለማሟላት የኢትዮ ጅቡቲ ኮሪደርን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የንግድ ኮሪደሩ ለኢትዮጵያና ጅቡቲ ኢኮኖሚ ትስስር ወሳኝ መስመር ከመሆን ባለፈ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ውህደትን በማስተዋወቅና በመፍጠር ረገድም ከፍተኛ አገልግሎት ላይ የሚገኝ መሆኑን አንስተዋል።
ኮሪደሩን ለስራ ማመቻቸት፣ የተቀናጀ አሰራር መፍጠር፣ አውቶሜሽን እና ዘመናዊነት እንዲሁም የንግድ ውህደትን ማሳደግ እንደሚያስፈልግም ገልፀው ለዚህም ኮንፍረንሱ አጋዥ እንደሚሆን ጠቁመዋል።
በኮንፍረንሱ የኢትዮጵያና ጅቡቲ መንግስታት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የንግድ መሪዎችና አመራሮች እንዲሁም አስመጪና ላኪዎችን ጨምሮ የዘርፉ ባለሙያዎች እየተሳተፉበት ይገኛል።
በታምራት ደለሊ