አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀገር አቀፍ ደረጃ የምግብ ሥርዓትና ኒውትሬሽን ስራዎችን ቅንጅታዊ አሰራር ለማጠናከር የሚያስችል ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፣ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) እንዲሁም ሌሎች የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
የምግብ ሥርዓትና ኒውትሬሽን ጥምር የሚኒስትሮች ስትሪንግ ኮሚቴ የጤና እና ግብርና ሚኒስቴሮች በጋራ የሚያስተባብሩትና 15 ሴክተር መስሪያ ቤቶችን ያካተተ ነው፡፡
ቅንጅታዊ አሰራርን ለማጠናከር ዓልሞ በተካሄደው ውይይትም÷ በሰቆጣ ቃልኪዳን ፕሮግራምና በኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓት ትራንስፎርሜሽንና ኒውትሬሽን ሴክሬተሪያት የተሰሩ ስራዎችና የተገኙ ተሞክሮዎች ቀርበው ምክክር ተደርጓል፡፡
በዚሁ ወቅት ዶክተር መቅደስ ዳባ÷ በጤናና በግብርና ሚኒስቴሮች እየታየ ያለው ቅንጅትና ለውጤት የመስራት ተነሳሽነት በጥሩ ደረጃ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የሰቆጣ ቃልኪዳን ፕሮግራም ውጤታማነቱ የታየና በፍጥነት ወደ ትግበራ በመግባት ለውጥ ያሳየ ፕሮግራም መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው እስከ አሁን የተሰሩ ስራዎችና የተገኙ ስኬቶች አበረታች መሆናቸውን በመግለጽ÷ በርካታ የሚቀሩ ስራዎች በመኖራቸው በቀጣይ ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር ለበለጠ ውጤታማነት መስራት አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡