አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ በኢትዮጵያ የርዋንዳ አምባሳደር ከሆኑት ቻርለስ ካራምባ ጋር ተወያዩ።
በውይይታቸውም በሁለቱ ሀገራት መንግስታዊ እንዲሁም ፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነት ዙሪያ መምከራቸው ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ የኮሪደር ልማት፣ አረንጓዴ ዐሻራ፣ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲሁም በምግብ ዋስትና ራስን ለመቻል የጀመረቻቸው ስራዎች አበረታች መሆናቸው በውይይቱ ተነስቷል።
ብልፅግና ፓርቲ በ1ኛው መደበኛ ጉባኤ ለመተግበር ቃል የገባቸው ጉዳዮች በአግባቡ እየተተገበሩ መሆኑን አቶ አደም አስረድተዋል፡፡
በዚህም በየዘርፉ ስኬቶች እየተመዘገቡ መሆኑን ጠቅሰው÷ በሁለተኛው የፓርቲው መደበኛ ጉባኤ የተገኙ ስኬቶችን የሚያስቀጥሉ ውሳኔዎች እንደሚጠበቁ አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች እንዲሁም ቀጣይ ግቦችና ራዕዮች ላይም ገለጻ ማድረጋቸውን የፓርቲው መረጃ አመላክቷል፡፡
አምባሳደሩ በበኩላቸው በፓርቲው ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ እንድንሳተፍ በመጋበዛችን እናመሰግናለን ብለዋል።
በጉባኤው ላይ የሚሳተፍ ልዑክ ከርዋንዳው ገዢ ፓርቲ አር ፒ ኤፍ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣም ገልጸዋል፡፡
የሀገራቱን ግንኙነት የሚያጠናክሩ የሁለትዮሽ ውይይቶች እንደሚደረጉም ተጠቅሷል፡፡