አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጃፓን፣ ሩሲያ እና ብሪታኒያ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል እያደረገች ያለውን እንቅስቃሴ እንደሚደግፉ አስታወቁ።
በጄኔቫና ኦስትሪያ የተባበሩት መንግሥታትና ዓለም አቀፍ ተቋማት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ፀጋአብ ክበበው÷ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅትን መቀላቀል በምትችልባቸው ጉዳዮች ላይ በድርጅቱ ከጃፓን፣ ሩሲያ እና ብሪታኒያ አምባሳደሮች እና ቋሚ ተወካዮች ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል።
በዚሁ ወቅትም ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን በምታደርገው እንቅስቃሴ ላይ አምባሳደሮቹ ላደረጉት ድጋፍ አምባሳደር ፀጋአብ አመስግነዋል።
ሀገራቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ጠንካራ ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ የኢንቨስትመንት እና የንግድ ግንኙነት አንስተው÷ የኢትዮጵያን የአባልነት ሂደት በተመለከተም ወቅታዊ መረጃዎችን አጋርተዋል።
ሂደቱ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ መግለጻቸውንም በጀኔቫ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል።
ልማታዊ እድገትን በማስቀደም ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት መመሪያ ጋር በሚጣጣም ሁኔታ እና የአባል ሀገራትን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ ሸቀጥ እና አገልግሎቶችን ለማቅረብ የሁለትዮሽ ድርድሮችን ለመጀመር ዝግጁ መሆኗንም ቷጋግጠዋል፡፡
የሀገራቱ አምባሳደሮች በበኩላቸው ኢትዮጵያ ሂደቱን አጠናክራ እንድትቀጥል አሳስበው ለመደገፍ ያላቸውንም ፍላጎት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን በምታደርገው እንቅስቃሴም ቴክኒካዊ ድጋፍ ለማድረግ ያላቸውን ቁርጠኝነት አስታውቀዋል።
በብርሃኑ አበራ