የሀገር ውስጥ ዜና

ለኢንዱስትሪዎች 369 ነጥብ 1 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ቀረበ

By yeshambel Mihert

January 23, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በግማሽ ዓመቱ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች 369 ሚሊየን 110 ሺህ ዶላር የውጭ ምንዛሪ መቅረቡን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት 16ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ሲሆን÷በዚህም የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል የሚኒስቴሩን የ2017 ግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን አቅርበዋል፡፡

በሪፖርታቸውም÷በግማሽ ዓመቱ ለተለያዩ አምራች ኢንዱስትሪዎች 9 ነጥብ 5 ሚሊየን ቶን በላይ ግብዓት ማቅረብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለሀገር እድገት፣ ለዘላቂ የሥራ እድልና ለንግድ ሚዛን መጣጣም የማይተካ ድርሻ አለው ብለዋል፡፡

ምቹ የልማት እቅዶችን በመጠቀም በተያዘው በጀት ዓመት አጋማሽ የዘርፉን ዘላቂ የእድገት ተስፋ የሚያሳዩ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡

በተለይም የማምረት አቅምን በማሳደግ፣ የሥራ እድል በመፍጠር፣ ገቢ ምርትን በመተካት፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን በማሸጋገር እንዲሁም ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር በማካሄድ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች ናቸው ብለዋል፡፡

በግማሽ ዓመቱ በጨርቃጨርቅ፣ በምግብና መጠጥ፣ በኬሚካልና ኮንስትራክሽን ዘርፍ 8 ሚሊየን 874 ሺህ ቶን ግብዓት ለማቅረብ ታቅዶ 9 ሚሊየን 527 ሺህ 593 ቶን ማቅረብ መቻሉን አመልክተዋል፡፡

በስድስት ወራት ውስጥ 468 ሚሊየን 420 ሺህ ዶላር የውጭ ምንዛሬ ለማቅረብ ታቅዶ 369 ሚሊየን 110 ሺህ ዶላር የውጭ ምንዛሪ መቅረቡን የጠቀሱ አቶ መላኩ÷ አፈፃፀሙ ከባለፈው ተመሳይ ወቅት ከቀረበው ጋር ሲነፃፀር 35 በመቶ እድገት ማስመዝገቡን ገልፀዋል፡፡