የሀገር ውስጥ ዜና

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የካሳንቺስ አያት የመኖሪያ መንደር ግንባታን አስጀመሩ

By yeshambel Mihert

January 23, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመንግስትና ግል አጋርነት በካሳንቺስ አያት የመኖሪያ መንደር 13 ሺህ 752 የመኖሪያ ቤቶችን ግንባታን በይፋ አስጀምረዋል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ እና በአያት ሪል ስቴት አጋርነት የሚገነቡት ቤቶች ለመኖሪያ ምቹ የሆኑ እና ሁሉንም የመሠረተ ልማቶች ያሟሉ እንደሚሆኑ ተጠቁሟል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት÷አስተዳደሩ የህብረተሰቡን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለማሟላት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም የህግ ማዕቀፎችን ማሻሻል መቻሉን በመግለጽ በመንግሥት እና በግል አጋርነት፣ በማህበር በመደራጀት፣ በግል እና በግል አጋርነት እንዲሁም በሪል ስቴት ቤቶችን ማልማት እንደሚቻል ተናግረዋል።

የካዛንቺስ አያት የመኖሪያ መንደርም የህዝቡን የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ለመመለስ ሁነኛ መፍትሔ እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡

በዛሬው ዕለትም በመንግሥት እና በአያት ሪል ስቴት አጋርነት 13 ሺህ 752 ቤቶች እንደሚገነቡ ጠቅሰው÷ ይህንንም በ18 ወራት ለማጠናቀቅ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

በካዛንቺስ አከባቢ የሚከናወኑ አጠቃላይ የመኖሪያ ቤት ግንባታዎች ሲጠናቀቁም ከ100 ሺህ በላይ ዜጎች የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ጠቁመዋል።

የአያት ሪል ስቴት ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ አብይ ማሞ በበኩላቸው÷የሚገነቡት መንደሮች የመኖሪያ ቤትን ጨምሮ የንግድ ሱቆች፣ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች፣ ትምህርት ቤት እና ጤና ጣቢያ እና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ያሟሉ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በግንባታው ሂደትም ከ10 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥርም መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡