የሀገር ውስጥ ዜና

የውጭ ሀገራት ገንዘብ የምንዛሬ ዋጋ በገበያ እንዲወሰን መደረጉ ወሳኝ ሪፎርም ነው – አቶ አቤ ሳኖ

By Meseret Awoke

January 23, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ሀገራት ገንዘብ የምንዛሬ ዋጋ በገበያ እንዲወሰን እና በሥርዓት እንዲመራ መደረጉ ትልቅና ወሳኝ ሪፎርም እንደሆነ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ ገለጹ፡፡

“የውጭ ሀገራት ገንዘብ ዋጋ በገበያ እንዲወሰን መደረጉ ያለው ኢኮኖሚያዊ አንድምታ” በሚል መሪ ሀሳብ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በኮንፈረሱ ላይ አቶ አቤ ሳኖ እንደገለጹት፤ የውጭ ሀገራት ገንዘብ እጥረትን ለመቅረፍ ተጨማሪ ገንዘብ ማተም የገበያውን እንቅስቃሴ ያዛባል።

የገንዘብ አጠቃቀም በህግና በሥርዓት እንዲመራ መደረጉ የውጭ ሀገራት ገንዘብ ዋጋ ተለዋዋጭ እንዳይሆን እና ገበያውን ለማረጋጋት አግዟል ብለዋል፡፡

የውጭ ሀገራት ገንዘብ የምንዛሬ ዋጋ በገበያ እንዲወሰን እና በሥርዓት እንዲመራ መደረጉም ትልቅና ወሳኝ ሪፎርም መሆኑን ተናግረዋል።

የውጭ ገንዘብ ክምችትን በማጠናከር የጥሬ ገንዘብ እጥረት እንዳይፈጠር በማድረግ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግራል ማለታቸውን በላቀ ደረጃ የባንኩ መረጃ ያመላክታል።

ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨትመንትን በማሳደግና ተለዋዋጭ የገበያ ሁኔታን በማረጋጋት ኢትዮጵያ በወጪ ንግድ ተወዳዳሪነቷ እንዲጨምር፣ የሀገር ውስጥ ምርትና ምርታማነትም እንዲያድግ የሚያግዝ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚስቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ጣሰው ወልደሀና (ፕ/ር)፤ ሪፎርሙ የሀገር ውስጥ ገንዘብ ክምችት እጥረትን በመፍታት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እንደሚደግፍ ተናግረዋል።

የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ጄነራል ፍቃዱ ፀጋ፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የተረጋጋ ገበያ የሚፈጥር በመሆኑ በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ ከፍተኛ ሚና መጫወት እንደሚችል አንስተዋል።