የሀገር ውስጥ ዜና

የአዳዲስ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታዎች በጥሩ አፈፃፀም ደረጃ ላይ መሆናቸውን ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ

By yeshambel Mihert

January 23, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በስድስት የተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተጀመሩ አዳዲስ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታዎች በጥሩ አፈፃፀም ደረጃ ላይ መሆናቸውን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ÷ በብልፅግና ፓርቲ አንደኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ለመተግበር ቃል በተገባው መሰረት በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራትና የተገኙ ውጤቶችን በማስመልከት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም ÷ በብልፅግና ፓርቲ አንደኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ለመተግበር ቃል በተገባው መሰረት በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት እምርታዊ ውጤት አስመዝግበዋል ብለዋል፡፡

በፓርቲው በተቀመጠ አቅጣጫ መሰረት ባለፉት ስድስት ዓመታት በዘርፉ የተደረጉ የለውጥ ሥራዎች የዜጎችን ተጠቃሚነት ያረጋገጡና ዘርፈ ብዙ ስኬቶች የተመዘገቡበት መሆኑን አንስተዋል።

የግል ባለሃብቶች በአነስተኛ አውሮፕላን ማረፊያዎች ግንባታ ላይ እንዲሳተፉ በመንግሥት የቀረበውን ጥሪ ተከትሎ የግንባታ ቦታዎችን የመለየትና ወደ ስራ ለማስገባት የዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡

የግሉን ዘርፍ በዓየር ትራንስፖርት ዘርፍ ማሳተፍ የሚያስችሉ አሰራሮችና የማበረታቻ ማዕቀፍ መዘርጋቱን ጠቅሰው ፥ ይህም በርካታ ባለሃብትን እየሳበ መሆኑን አንስተዋል።

በትናንሽ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ የግል ባለሃብቶች እንዲሳተፉ መንግሥት ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ በዘርፉ ለመሳተፍ ጥያቄ ያቀረቡ መኖራቸውንም ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።

ለዚህም ቦታዎችን በመለየት እንዲሁም በግንባታው ለሚሳተፉ ባለሃብቶች የቴክኒክ ድጋፍ የመስጠትና ወደ ሥራ ለማስገባት የዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

የአየር ትራንስፖርት ደህንነትን አስተማማኝ ከማድረግ አኳያም የአቪየሽን ዘርፉን በሁሉም ረገድ የማዘመንና የማጠናከር ስራዎች መከናወኑን በመግለጽ ፤ አዳዲስ አውሮፕላኖች ግዢ በመፈፀምና ወደ ስራ በማስገባት በዘርፉ አገልግሎት አሰጣጥና ተደራሽነትን በማስፋት ረገድ የላቀ ውጤት ተመዝግቧል ነው ያሉት፡፡

ከሎጂስቲክስ ጋር በተያያዘ ኢኮኖሚውን ማሳለጥ የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑን መናገራቸውን የብልፅግና ፓርቲ መረጃ ያመላክታል፡፡

የሞጆ ደረቅ ወደብ ማስፋፊያ ግንባታ 80 በመቶ መድረሱም የተገለጸ ሲሆን ÷ ለባህር አገልግሎት መሳለጥ የአንድ መርከብ ግዢ እንደተፈጸመም ተመላክቷል፡፡