የሀገር ውስጥ ዜና

በኮንትራት ፋርሚንግ ከለማው ማሳ ከ37 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል

By ዮሐንስ ደርበው

January 24, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሁሉም ክልሎች በ2016/17 የምርት ዘመን በግብርና ምርት ውል (ኮንትራት ፋርሚንግ) ከለማው ማሳ 37 ሚሊየን 990 ሺህ 82 ኩንታል ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ይህ ምርት የሚጠበቀው በኮንትራት ፋርሚንግ ከለማው 2 ሚሊየን 121 ሺህ 350 ሔክታር ማሣ መሆኑን በሚኒስቴሩ የግብርና ምርት ውል ዴስክ ኃላፊ ሱልጣን መሐመድ ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡

በዚህም ሰሊጥ፣ አኩሪ አተር፣ ቦለቄ፣ ማሾ እና ኑግን ጨምሮ በገበያ ተፈላጊ የሆኑ ሰብሎች መልማታቸውን ጠቁመዋል።

ሰሊጥ 8 ሚሊየን 418 ሺህ 637፣ አኩሪ አተር 8 ሚሊየን 903 ሺህ 175፣ ቦለቄ 5 ሚሊየን 507 ሺህ 95፣ ማሾ 1 ሚሊየን 335 ሺህ 501 እና ኑግ 279 ሺህ 52 ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅም አብራርተዋል፡፡

እንዲሁም ሽምብራ 1 ሚሊየን 188 ሺህ 744፣ ባቄላ 234 ሺህ 901፣ በቆሎ 677 ሺህ 280፣ ሩዝ 62 ሺህ 310፣ የዳቦ ስንዴ 7 ሚሊየን 5 ሺህ 827፣ ዱረም ስንዴ 178 ሺህ 892፣ ገብስ 3 ሚሊየን 412 ሺህ 97፣ እርግብ አተር 501 ሺህ 683፣ ማሽላ 61 ሺህ 440፣ ጤፍ 204 ሺህ 382፣ ለውዝ 8 ሺህ 500 እና ሱፍ 10 ሺህ 566 ኩንታል ምርት ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ከላይ በተጠቀሰው ጊዜ ሰብሉን በማልማት እና ምርቱን በመሰብሰብ ሂደት 1 ሺህ 819 አስመራቾች እና 1 ሚሊየን 4 ሺህ 870 አምራች አርሶ አደሮች መሳተፋቸውንም ገልጸዋል፡፡

ምርቱ በያዝነው ወር መጨረሻ ተሰብስቦ እንደሚጠናቀቅም ጠቁመዋል፡፡

የኮንትራት ፋርሚንግ አርሶ አደሮች እና ገዥዎች የግብርና ምርት ገበያ ላይ ተመስርተው አስቀድመው ስምምነት የሚፈጥሩበት መንገድ ሲሆን÷ ስምምነቱ የአርሶ አደሮች የክፍያ ዋጋ፣ ለገዥዎች የሚቀርበው የምርት መጠን፣ ጥራት እና የመቅረቢያ ወቅት ተለይቶ የሚቀመጥበት ነው።

በዮሐንስ ደርበው