የሀገር ውስጥ ዜና

የአፍሪካ ሕብረት ጉባዔ ስኬታማ እንዲሆን ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ

By ዮሐንስ ደርበው

January 24, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) 38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ እና 46ኛው የሚኒስትሮች ስብሰባ ስኬታማ እንዲሆን በቂ ዝግጅት መደረጉን ፌደራል ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የልዩ (ቪአይፒ) ፕሮቶኮል አጃቢዎች እና የአሽከርካሪዎች ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል፡፡

በዚሁ ወቅት ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል÷ 38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ እና 46ኛውን የሚኒስትሮች ስብሰባ እንዲሳካ ከወዲሁ በቂ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡

ጉባዔው የተሳካ እንዲሆን ተቋሙ የታጠቃቸው ድሮኖችና ሌሎች ዘመኑን የሚመጥኑ ቴክኖሎጂዎች ሥራ ላይ ይውላሉ ብለዋል፡፡

የሰው ኃይሉን በሀገር ውስጥ፣ በቻይና፣ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች በማሰልጠን እና የፀጥታ ሥራውን በማዘመን ከፍተኛ ዝግጅት መደረጉን አረጋግጠዋል፡፡

ተመራቂዎቹ በስልጠና ያገኙትን ዕውቀትና ክኅሎት ተግባር ላይ በማዋል፣ በጥብቅ ዲሲፕሊንና በቅንጅት በመስራት አምባሳደር ሆነው የኢትዮጵያን ገፅታ ከፍ በማድረግ የሕብረቱ ጉባዔ የተሳካ እንዲሆን እንዲተጉ የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል።

ተመራቂዎቹ ከ55 ተቋማት የተውጣጡ መሆናቸውን የፌደራል ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡