የሀገር ውስጥ ዜና

359 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል

By Feven Bishaw

January 24, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሊባኖስ እና በሳዑዲ ዓረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 359 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው መመለሳቸው ተገለፀ፡፡

 

በሊባኖስ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ እና ለአደጋ የተጋለጡ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገር የመመለስ ስራ እንደቀጠለ ሲሆን÷ በሳምንቱ 156 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።

 

ከእነርሱ ውስጥ 143ቱ ሴቶች፣13ቱ ጨቅላ ህፃናት እንዲሁም 18ቱ እድሜያቸው ከ18 አመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ናቸው።

 

እንዲሁም በሳምንቱ 203 ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ ዓረቢያ ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ሲሆን÷ከተመላሾች መካከል 4ቱ እድሜያቸው ከ18 አመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች መሆናቸው ታውቋል።

 

ለተመላሽ ዜጎች በአውሮፕላን ማረፊያና በማቆያ ማዕከላት ተገቢውን ድጋፍ እና እንክብካቤ የማድረግ እና ከቤተሰብ ጋር የማቀላቀል ስራም እየተሰራ እንደሚገኝ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል ፡፡

 

ከሚያዚያ 4 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ እየተከናወነ በሚገኘው ከሳዑዲ ዓረቢያ ዜጎችን የመመለስ ስራ እስካሁን 90 ሺህ 101 ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገር መመለስ ተችሏል።