አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የባንክ አሰራርን በመተላለፍ ያለአግባብ ከ22 ሚሊየን ብር በላይ ክፍያ እንዲፈጸም በማድረግ የሙስና ወንጀል የተከሰሱ አራት ግለሰቦች በጽኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት ወሰነ።
የቅጣት ውሳኔ የተላለፈባቸው ተከሳሾች 1ኛ የአቢሲኒያ ባንክ ሲኤምሲ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ የነበረ ኤፍሬም ጎሳዬ፣ 2ኛ የቅርንጫፉ ኦፕሬሽን ስራ አስኪያጅ የነበረች ሄርሜላ አብዱ፣ 3ኛ የፕሩደንስ ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማህበር ስራ አስኪያጅ ደስታ ጥላሁን እና 4ኛ ተከሳሽ ፕሩደንስ ትሬድንግ ኃ/የተ/የግ/ማህበር ናቸው።
የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ተከሳሾች ላይ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 5 ንዑስ ቁጥር 4 እንዲሁም አንቀጽ 9 ንዑስ ቁጥር 1/ሀ እና ንዑስ ቁጥር 2 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ መተላለፍ የሚል የወንጀል ክስ አቅርቦባቸው ነበር።
በዚህም ክስ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች በቅርንጫፉ ስራ አስኪያጅ እና ኦፕሬሽን ስራ አስኪያጅ ሆነው ሲያገለግሉ በልዩ ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ ከሆኑት ከ3ኛ እና ከ4ኛ ተከሳሽ ጋር በመመሳጠር የባንኩን አሰራርና መመሪያ በመተላለፍ የፕሩደንስ ማህበር የባንክ ሂሳብ ውስጥ 1 ሺህ ብር ብቻ ባለበት እና ማህበሩ የክፍያ ማዘዣ ሰነድ ለማሰራት የሚያስችል በቂ ገንዘብ በሌለበት ሁኔታ ላይ የተሰጣቸውን ያለአግባብ አገልግሎት እንዲያገኝ ማድረጋቸው በክሱ ዝርዝር ላይ ተጠቅሷል።
ለሞባይል ቫውቸር ካርዶችን ለመግዛት በሚል ምክንያት1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ከ3ኛ እና ከ4ኛ ተከሳሾች ጋር በመመሳጠር በመስከረም 5 ቀን 2014 ዓ.ም 4ኛ ተከሳሽ ከሆነው ድርጅት ሂሳብ ላይ በቂ ገንዘብ ሳይኖርና ሳይቀነስ ወይም በጥሬ ገንዘብ ክፍያ ሳይፈፀም እንዲሁም በሲስተም ላይ ሳያልፍ አምስት ሲፒኦዎችን ያለአግባብ አዘጋጅተው በመስጠት፤ በህገ ወጥ መንገድ በተዘጋጁ በአምስት ሲፒኦዎች 22 ሚሊየን 800 ሺህ ብር ባንኩ እንዲከፍል ማድረጋቸው ተጠቅሷል።
በዚህም በባንኩ ላይ ጉዳት እንዲደርስ እና በዚሁ የገንዘብ መጠን ልክ ከፍተኛ ጥቅም ያገኙ መሆኑ ተጠቅሶ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት 3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች በልዩ ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት በሥልጣን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡
ከ1ኛ ተከሳሽ ውጪ ያሉ ተከሳሾች ችሎት ቀርበው ክሱ ከደረሳቸውና ወንጀሉን አልፈጸምንም ብለው ክደው በመከራከራቸው ዐቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃ አቅርቧል።
ፍርድ ቤቱ ማስረጃውን መርምሮ እንዲከላከሉ በሰጠው ብይን መከላከል አለመቻላቸውን ጠቅሶ የጥፋተኝነት ፍርድ ሰጥቶባቸዋል።
በዚህም የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት መርምሮ በአንድ ዳኛ የሃሳብ ልዩነት በአብጫ ድምጽ መካከለኛ ደረጃ የያዘ ሲሆን አንድ ዳኛ ደረጃው ከፍተኛ መሆን እንዳለበት ጠቅሰው የሀሳብ ልዩነታቸውን አቅርበዋል።
ከዚህ በኋላ 1ኛ ተከሳሽ በ8 ዓመት ጽኑ እስራትና በ40 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ የወሰነ ሲሆን 2ኛ ተከሳሽን ደግሞ 5 የቅጣት ማቅለያ በመያዝ በ5 ዓመት ከ6 ወራት ጽኑ እስራትና በ7 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንድትቀጣ ወስኗል።
የማህበሩ ስራ አስኪያጅ የሆነውን 3ኛ ተከሳሽን በሚመለከት በ6 ዓመት ጽኑ እስራትና በ10 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ የወሰነ ሲሆን 4ኛ ተከሳሽ ማህበሩን ደግሞ በ440 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ውሳኔ ሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ