አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ለሕዝቡ የቅሬታ ምንጭ የሆኑ ጉዳዮችን መፈተሽ፣ የአገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል፣ ቡድንተኝነት እና ብልሹ አሠራርን ፈጥኖ ማረም ይገባል ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የክልሉ መሥተዳድር ምክር ቤት ባካሄደው 22ኛ መደበኛ ጉባዔ የሥድስት ወራት ዕቅድ አፈፃፀምን ገምግሞ አጽድቋል፡፡
ተቋማት ከሚመለከታቸው እና ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ ቅንጅታዊ ስራን ለመተግበር የጀመሩት ጥረት ውጤታማ መሆኑን ርዕሰ መሥተዳድሩ ጠቁመዋል።
በየደረጃው ተግባራዊ የሚሆነው እቅድ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል እና በጠንካራ ጉዳዮች ላይ የተመሰረተ ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
በሁሉም ስራ ላይ አሳታፊነት እያደገ በመጣ ቁጥር ውጤታማ መሆን እንደሚያስችል ጠቅሰው፤ የግማሽ ዓመቱ አፈጻጸም አበረታች መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሕዝብን ተጠቃሚነት እየገመገሙ መሄድ እና ተሳትፎውን ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመው÷ የሚቀርቡ አዳዲስ ፍላጎቶችን ማስተናገድ የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በሚቀጥሉት ስድስት ወራት የሕዝብ ተጠቃሚነትን ማሳደግ ላይ ማተኮር ይጠበቃል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡
መንግስታዊ አገልግሎትን በአዳዲስ አስተሳሰብ እና ፈጠራ ላይ በመመስረት መስራት አለብን፤ የመልካም አስተዳደር ችግሮችንም ነቅሶ መፍታት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡