አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በብራዚል የኢትዮጵያ አምባሳደር ልዑልሰገድ ታደስ ከብራዚል የዓሣ ሃብት ሚኒስትር ጋር በዘርፉ በትብብር ለመሥራት ያለመ ምክክር አድርገዋል፡፡
አምባሳደሩ ከብራዚል የዓሣ ሃብት ሚኒስትር አንድሬ ዳ ፓውላ ጋር ባደረጉት ውይይት÷ የዓሣ ሃብትን ለማልማት የሚያስችል ትብብር ለመፍጠር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡
የዓሣ ሃብት ልማት በኢትዮጵያ የልማት ፖሊሲ ትኩረት ከተሰጣቸው የዕድገት ዐቅሞች መካከል መሆኑንም አሥረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍን በማዘመንና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበመሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በመስኩ ከብራዚል ጋር የሚፈጠር ትብብር ለቀጣይ ዕድገት ወሳኝ ድርሻ እንደሚኖረውም መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
ሚኒስትሩ በበኩላቸው ሀገራቱ በግብርናው ዘርፍ ያላቸው ትብብር በዓሣ ሃብት ልማት እንዲጠናከር እንፈልጋለን ብለዋል፡፡
ሀገራቸው በዓሣ ሃብት ልማት ያካበተችውን ልምድ፣ ቴክኖሎጂ እና ዕውቀት በሁለትዮሽ ትብብር እና በብሪክስ ማዕቀፍ ለኢትዮጵያ ለማካፈል ዝግጁ መሆኗንም አረጋግጠዋል፡፡