የሀገር ውስጥ ዜና

የኮሪደር ልማቱ የጅማ ከተማን የተደበቀ ውበት ይበልጥ እንዲፈካ አድርጓል – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

By Melaku Gedif

January 25, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኮሪደር ልማቱ የጅማ ከተማን የተደበቀ ውበት ይበልጥ እንዲፈካ አድርጓል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጅማ የነበራቸውን ቆይታ አስመልከተው በሰጡት ማብራሪ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብት የታደለች ሀገር መሆኗን አውስተው÷ ቢሰራባቸው ዓለምን የሚያስደንቁ የተፈጥሮ ጸጋዎች በሁሉም የኢትዮጵያ ጫፍ እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ መደመር የሚለው ሃሳብ ሲጀመር ሶስት ዋና ዋና ምሰሶዎች ላይ የቆመ እንደነበር የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ የመጀመሪያው የኢትዮጵያን ተፈጥሮ፣ ጸጋና ሃብት በውል ማወቅ መቻል ነው ብለዋል፡፡

አሁን ላይ የጅማን የተፈጥሮ አቅም በመረዳት የተሰራው ሥራ የሚያስደምም መሆኑን ጠቅሰው÷ ይህም የሃሳብ ፈጠራ፣ የሥራ ዲሲፕሊን እና የነዋሪዎች ሃሳቡን መደገፍ በጥምረት ያስገኙት ውጤት ነው ብለዋል፡፡

የጅማ ሕዝብ የከተማዋን ልማት በቅንነት ተቀብሎ ያደረገው ሁለንተናዊ ድጋፍ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው÷ ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ሃሳብ አለን፣ የመስራት ትጋት አለን፣ ብርታት አለን፤ ጥሩ ተከታይ ካገኘን፣ ከተደመርንና ከተሰናሰልን በጅማ ከተማ ያየነው አይነት ውበት በሌሎችም ይበልጥ ይገለጣል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ጅማ ውብ፣ ታሪክ ጠገብ እና ሰላም ወዳድ ከተማ ነበረች፤ አሁን ደግ ዘመን መጥቶላት፣ ጊዜና ሁኔታ ተመቻችቶላት የተደበቀው ውብቷ እንዲፈካ ሁኗል ብለዋል፡፡

በጅማ የታየውን ስራ አርባምንጭን ጨምሮ በሌሎች ከተሞች ጨከን ብለን መተግበር አለብን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷በዚህም የሰለጠኑ ከተሞችን መፍጠር ይቻላል ብለዋል፡፡፡

ሃሳብ የሌላቸው ሰዎች ያልተጨበጠ ነገር ከሚያወሩ ሃሳብን ተከትለው ቢሰሩ አሊያም አማራጭ ሃሰብ አምጥተው ለልጅ ልጆች መልካም ነገር ቢያወርሱ የተሻለ ነው ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ