አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በ75 ሚሊየን ብር የተገነባው የፈሳሽ ናይትሮጅን ማምረቻ ፋብሪካ ተመርቆ ሥራ ጀምሯል፡፡
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሃሰን፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷የተመረቀው የፈሳሽ ናይትሮጅን ማዕከል በክልሉ የመጀመሪያ መሆኑን ተናግረዋል።
ክልሉ በእንስሳት ሀብት የታደለ ቢሆንም የፈሳሽ ናይትሮጂን ዩኒት ባለመኖሩ በዘርፉ ተፈላጊውን ውጤት ማስመዝገብ አለመቻሉን ጠቁመው÷ፋብሪከው የእንስሳት ዘርፉን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶና አርብቶ አደሩን ሕይወት በዘላቂነት ለመቀየር እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ከለውጡ ወዲህ በመላ ሀገሪቱ የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ብልፅግና ሊያረጋግጡ የሚችሉ በርካታ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
የፕሮጀክቶች አፈጻጸም ባህል እየተሻሻለ መምጣቱን ጠቁመው÷ያለንን የእንስሳት ሃብት በቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ ምርትና ምርታማነቱን ለመጨመር እየተሠራ ነው ብለዋል።
ሚኒስቴሩ ክልሉን ጨምሮ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የአርሶ እና አርብቶ አደሩን የአኗኗር ዘይቤ ለመቀየር እና በአየር ፀባይ ለውጥ የሚመጡ ችግሮችን በመለየት ምላሽ ለመስጠት በትኩረት እየሠራ ነው ማለታቸውን የክልሉ ኮመኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።