የሀገር ውስጥ ዜና

ብልፅግና ፓርቲ የዜጎችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ተጨባጭ ውጤት አስመዝግቧል – ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)

By Mikias Ayele

January 26, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ)

ብልፅግና ፓርቲ በመጀመሪያ ጉባኤው በገባው ቃል መሰረት የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቡን የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ሚኒስትሯ እንደገለፁት፣ ፓርቲው የሴቶችንና ወጣቶችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲሁም ፖለቲካዊ ተሳትፎ ማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራትን አከናውኗል።

በኢትዮጵያ ሴቶች በህግ አውጪ፣ በህግ ተርጓሚውና ህግ አስፈፃሚ አካላት ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ ከለውጡ በፊት ከነበረበት 23 በመቶ ወደ 35 በመቶ ማደጉን ተናግረዋል፡፡

ዜጎች በመረጡት አደረጃጀት የመደራጀት መብትና ጥቅማቸውን ማስከበር እንዲችሉ ፓርቲው ባከናወናቸው ተግባራት የመደራጀት ምጣኔ ከ10 ወደ 40 በመቶ ማደጉን ነው የተናገሩት፡፡

በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሱ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በመከላከል ረገድ ዓለም አቀፍ እውቅና የተገኘበት ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን ገልጸው፤ በገጠር ጎጂ ድርጊቶች የማይፈምባቸው ቀበሌዎች ቁጥር ከ1 ሺህ በላይ መሆኑን ተናግረዋል።

ከለውጡ በኋላ በገጠር የሴቶች የመሬት ባለቤትነት ከ38 ወደ 62 በመቶ ማደጉን ጠቅሰው፤ የቁጠባ አቅማቸውን ከ16 በመቶ ወደ 49 በመቶ ማሻሻል እና የቆጠቡትን በአግባቡ መጠቀም መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

ህፃናት ቀጣይ የኢትዮጵያ የብልፅግና መሰረቶች መሆናቸውን በመገንዘብ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሯ÷ እስከ ቀበሌ ባለው አደረጃጀት የህፃናት ፓርላማ በማደረጃት ህፃናት ድምፃቸው የሚሰማበት ሥርዓት መፍጠር ተችሏል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ወጣቶችን ለማብቃት በተከናወኑ ተግባራት ፖለቲካዊ ተሳትፏቸውን ከ10 በመቶ ወደ 18 በመቶ ከፍ ማድረግ መቻሉን ማብራራታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግም ሀገር አቀፍ የወጣቶች ካውንስል እንዲመሰረት መደረጉንም ገልጸዋል።