የሀገር ውስጥ ዜና

አስተዳደሩ ወላጅ አልባ ህፃናትን አሳድጎ ለወግ ማዕረግ እንዲበቁ ያደርጋል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

By Mikias Ayele

January 26, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወላጅ አልባ ህፃናትን ከማሳደግ ባለፈ ለወግ ማዕረግ እንዲበቁ ያደርጋል ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ፡፡

ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ በኮልፌ የወንዶች ልጆች ማሳደጊያ እና በቀጨኔ የሴቶች ማሳደጊያ ማዕከል ካሳደግናቸው ልጆቻችን መካከል ሰባቱን ለወግ ለማዕረግ አብቅተን የጋብቻ ስነ ስርዓታቸውን ለመፈጸም በቅተናል ብለዋል፡፡

ሙሽሮች ፈጣሪ በህይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ረድቷችሁ ለዚህ ለተባረከ እና ለተቀደሰ የህይወታችሁ ምዕራፍ ቀን እንኳን አደረሳችሁ ያሉት ከንቲባዋ፤ ለጥነዶቹ መልካም ጋብቻን ተመኝተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወላጅ ለሌላቸዉ ወላጅ እና ቤተሰብ በመሆን አሳድጎ ለወግ ለማዕረግ እንዲበቁ ከማድረግ በተጨማሪ በቀጣይ የህይወታቸው ምዕራፍ የስራ እድል እንደሚፈጥርላቸውም እና የተሳካ ህይወት እንዲመሩ የሚያግዝ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ለዚህ የተቀደሰ ተግባር መሳካት ትብብር ላደረጉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል፡፡