የሀገር ውስጥ ዜና

የምክር ቤቱ ልዩ ስብሰባ እየተካሄደ ነው

By Mikias Ayele

January 27, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ ልዩ ስብሰባ እየተካሄደ ነው፡፡

ምክር ቤቱ በስብሰባው የግብርና ሚኒስቴርን የ2017 በጀት ዓመት የሥድስት ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት እያዳመጠ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በስብሰባው ማጠቃለያ ሁለት የብድር ስምምነቶች እንደሚጸድቁ ይጠበቃል መባሉን የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡

የከተማ መሬት ይዞታ እና መሬት ነክ ንብረት ምዝገባ እንዲሁም የከተማ መሬትን በሊዝ ስለመያዝ የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅን አስመልክቶ የከተማ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚያቀርበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ መርምሮ አዋጁን እንደሚያፀድቅም ይጠበቃል ተብሏል።

በተጨማሪም የአጠቃላይ ትምህርት ረቂቅ አዋጅን አስመልክቶ የሰው ሀብት ልማት፣ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ መርምሮ አዋጁን ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡