የሀገር ውስጥ ዜና

በሲዳማ ክልል የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ተጀመረ

By Melaku Gedif

January 27, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 19 ፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሲዳማ ክልል የዘንድሮ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በዛሬው ዕለት በይፋ ተጀምሯል።

የተፋሰስ ልማት ስራው የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በሰሜናዊ ሲዳማ ዞን ቦርቻ ወረዳ አልዳዳ ደላ ቀበሌ ነው የተጀመረው።

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ሃላፊ አማካሪ አቶ አክሊሉ አዱላ÷ ባለፉት ዓመታት በተሰራው ስራ ከፍተኛ ውጤት እየመጣ መሆኑን አመላክተዋል።

የተፋሰስ ልማቱ የውሃ ክምችትን በማሳደግና የመሬት ለምነትን በማጎልበት የበጋ መስኖ ስራው እንዲሳለጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስታውቋል።

በዘንድሮው አፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በ678 ንዑስ ተፋሰሶች 136 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ እንደሚከናወን ተናግረዋል፡፡

የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራው ለተከታታይ 30 ቀናት የሚካሄድ ሲሆን÷ በዚህም ከ1 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ይሳተፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተጠቁሟል፡፡

በብርሃኑ በጋሻውና በደብሪቱ በዛብህ