የሀገር ውስጥ ዜና

በግብርና ምርታማነት ላይ ዕድገት ተመዝግቧል- አቶ አሻድሊ ሀሰን

By ዮሐንስ ደርበው

January 27, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከለውጡ ወዲህ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጠ በተከናወኑ ሥራ ስኬቶች መመዝገባቸውን የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።

የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ በቴክኖሎጂ በመደገፍ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውንም አንስተዋል፡፡

የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ሊያረጋግጡ የሚችሉ ኢኒሼቲቮች ከመተግበር ባለፈ ጠንካራ የሥራ ባሕል እንዲኖር በትኩረት ሲሠራ ቆይቷል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡

ዓመታዊ የምርታማነት አቅም ከነበረበት 18 ሚሊየን ኩንታል ወደ 45 ሚሊየን ማሳደግ መቻሉንም ተናግረዋል፡፡

የአርሶ አደሩ የግብዓት አጠቃቀም ባሕል እና የግብርና ሜካናይዜሽን ተጠቃማነትን በማሻሻል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት መደረጉንም አውስተዋል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት ከ500 ሚሊየን በላይ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያላቸው እና ለክልሉ ሥነ-ምኅዳር ተስማሚ የሆኑ ችግኞች መተከላቸውን ጠቅሰው÷ ከዚህ ውስጥ 85 በመቶው መጽደቁን አረጋግጠዋል፡፡