የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ ለህብረቱ ተቋማዊ ማሻሻያ አጀንዳ ስኬታማ ትግበራ ቁርጠኛ ናት – ፕሬዚዳንት ታዬ

By Mikias Ayele

January 27, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ህብረት ተቋማዊ ማሻሻያ አጀንዳ ስኬታማ ትግበራ ቁርጠኛ መሆኗን አረጋገጡ።

በኬኒያ ናይሮቢ በተካሄደው የአፍሪካ ህብረት ተቋማዊ ማሻሻያ ስብሰባ ላይ ፕሬዚዳንት ታዬ ባደረጉት ንግግር፤ ህብረቱ እስካሁን ያከናወናቸውን ተቋማዊ ማሻሻያዎች አድንቀዋል።

የአህጉሪቱን ዕምቅ አቅም በመጠቀም ረገድ አሁንም ከፍተኛ ትኩረት የሚሹ ተግዳሮቶች እንዳሉም ጠቁመዋል፡፡

ህብረቱ በጥሩ መሰረት ላይ ተደላድሎ ሊቆም የሚችለው 75 በመቶውን የፕሮግራሞች በጀት መሸፈን እና 25 በመቶውን የሰላም ጉዳዮችን ለመከወን የተቀመጡ ግቦችን ማሳካት ሲቻል ነው ብለዋል፡፡

በቅርቡ የታደሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መንግስት የቀደሙ አፍሪካውያን የአፍሪካ ህብረትን ለመመስረት ያደረጉትን ከፍተኛ ትኩረት፣ ትጋት እና ራዕይ የሚያስታውስ መሆኑን አውስተዋል።

በህብረቱ ተቋማት የተደረጉ የማሻሻያ ርምጃዎች እውቅና ሊሰጣቸው እንደሚገባ ገልጸው፤ የህብረቱን አቅም በተሟላ ሁኔታ ለመገንባት ፈታኝ ቀሪ የቤት ሥራዎች እንዳሉ አመላክተዋል።

በመሆኑም አካታችነት፣ የፋይናንስ ሉዓላዊነት፣ ለኅብረቱ አጀንዳዎች ቅድሚያ መስጠትና ማቀናጀት፣ ጠንካራ የውይይት ባህልን ማዳበር እንዲሁም የህብረቱን ውጥኖች ሂደት እና ትስስር በዓለም አቀፍ ደረጃ ማጉላት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ 27-19-2023 ላይ ተመርኩዞ በተዘጋጀው የህብረቱ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ማስፈፀሚያ የሚሆን ተገማች እና ዘላቂነት ያለው የፋይናንስ ድጋፍ በማገኘት ረገድ የተከናወኑ ተግባራትን አድንቀዋል፡፡

በዚህ ረገድ የአፍሪካ ህብረት ራሱን የቻለ የሰላም ድጋፍ ማስፈፀሚያ ዳይሬክቶሬት ያስፈልገዋል ያሉት ፕሬዚዳንት ታዬ፤ መዋቅሩን በአስቸኳይ መዘርጋት ያስፈልጋል ብለዋል።

የአፍሪካ ህብረት ተቋማዊ ማሻሻያ አጀንዳዎችን በውጤታማነት በመተግበር ተጨባጭ ውጤት ለማስመዝገብ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት የተጠናከረ እና የተቀናጀ ጥረት ማድረግ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

የአፍሪካ ህብረት ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ጠንካራ፣ የተቀናጀ እና ህብረቱ ውጤታማ ተቋም ሆኖ እንዲወጣ ለማድረግ የተቀናጀ ርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ህብረት ተቋማዊ ማሻሻያ አጀንዳ ሙሉ ድጋፍ እንደምትሰጥም አረጋግጠዋል።