የሀገር ውስጥ ዜና

ማህበሩ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የሰብዓዊነት ት/ቤት ከፈተ

By Melaku Gedif

January 27, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የሰብዓዊነት ት/ቤት መክፈቱን ይፋ አድርጓል፡፡

በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ሎሚ በዶን ጨምሮ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅት ተወካዮችና አምባሳደሮች ተገኝተዋል።

ምክትል አፈ ጉባዔ ሎሚ በዶ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት÷ የሰብዓዊነት ትምህርት ቤቱ በሰብዓዊ እርዳታ ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ሃብት ለማፍራት የጎላ ሚና ይኖረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ለበርካታ ዓመታት በተፈጥሮም ሆነ ሰው ሰራሽ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ልዩ ልዩ ሰብዓዊ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

የሰብዓዊነት ትምህርት ቤቱ ሰብዓዊነትን የተላበሰ ትውልድ ለማፍራትና በተለያዩ ምክንያቶች ለሚከሰቱ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የጎላ ሚና እንደሚኖረውም ገልጸዋል፡፡

ማህበሩ የሰብዓዊነት ተግባሩን በበለጠና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚረዳው ምክትል አፈ ጉባኤዋ ጠቅሰዋል፡፡

በመሆኑም መንግስት ማህበሩ ያቀደውን ተግባር እንዲያሳካ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ዋና ጸሃፊ አበራ ሉለሳ በበኩላቸው÷ የትምህርት ቤቱ ዋና አላማ በሰብዓዊነት የታነጸ ትውልድ ማፍራት ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የትምህርት ካሪኩለሙ ተዘጋጅቶ ማለቁንና ከነገ ጀምሮ ምዝገባ የሚካሔድ መሆኑን ነው ያመላከቱት፡፡