የሀገር ውስጥ ዜና

የአዲስ አበባ ትራንስሚሽንና ዲስትሪቢዩሽን መልሶ ግንባታ ፕሮጀክትን በያዝነው ዓመት ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው

By ዮሐንስ ደርበው

January 28, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እየተከናወነ የሚገኘውን የአዲስ አበባ ትራንስሚሽንና ዲስትሪቢዩሽን መልሶ ግንባታና አቅም ማሳደግ ፕሮጀክት በያዝነው በጀት ዓመት ለማጠናቀቅ እየሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ በ50 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውስጥ የዲስትሪቢዩሽን መስመሮች አቅም በማሳደግ ተጨማሪ የኃይል ፍላጎቶችን እንዲያስተናግድ ለማስቻልና የኃይል ብክነትን ለመቀነስ እንዲሁም መሰረተ ልማቱን ከአንድ ማዕከል ሆኖ ለመቆጣጠር የሚያስችለው ፕሮጀክት 87 ነጥብ 94 በመቶ ሥራው መጠናቀቁንም አገልግሎቱ አስታውቋል፡፡

ፕሮጀክቱ ረጅም ጊዜ ያገለገሉ የእንጨት ምሰሶዎችን በኮንክሪት መቀየርን ጨምሮ መስመሮቹን በተሻለ ጥራት በማደስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የኃይል ፍላጎት እንደሚያረካ እና ከመስመሮች እርጅና ጋር ተያይዞ የሚፈጠርን የኃይል መቆራረጥ በእጅጉ እንደሚቀንስ ይታመናል ብሏል፡፡

እስከ አሁንም 9 ሺህ 644 የእንጨት ምሰሶዎች በኮንክሪት ምሰሶ ተቀይረው፤ 347 ነጥብ 39 ኪሎ ሜትር በቀላል ንክኪ ምክንያት ኃይል እንዳይቋረጥ የሚያደርጉ ሽፍን የመካከለኛ መስመር ዝርጋታ መከናወኑን ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡

በተለያዩ ምክንያቶች የኃይል መቆራረጥ ቢፈጠር እንኳ መሥመሩን ከአንድ ቦታ ሆኖ ለመቆጣጠር የሚያስችል ቴክኖሎጂን ያካተተ በመሆኑ፤ ችግሩ የተፈጠረበትን ትክክለኛ ቦታ ያመላክታል ነው ያለው፡፡

ይህ ቴክኖሎጂ በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ በ50 ኪሎ ሜትር ራዲየስ የሚገኙ 41 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎችንና 226 መለስተኛ መቆጣጠሪያ ጣቢያዎችን የሚያገናኝ ቴክኖሎጂ መሆኑን የገለጸው አገልግሎቱ÷ ሥራው 65 በመቶ መጠናቀቁን አመላክቷል፡፡

ከዚህ ባሻገር አራት አዳዲስ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ተገንብተዋል፤ ለአምስት ነባር የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች የአቅም ማሳደግ ሥራ ተሰርቶላቸው አገልግሎት እየሰጡ ነው ብሏል፡፡ አንድ አዲስ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ በግንባታ ሂደት ላይ እንደሚገኝም ነው የገለጸው፡፡

ሥራቸው ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት የጀመሩት የፕሮጀክቱ ሥራዎች ከዚህ ቀደም ከነበረው ጋር ሲነፃፀር የኃይል መቆራረጥ ድግግሞሽን ቀንሰውታል ሲልም ገልጿል፡፡