የሀገር ውስጥ ዜና

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የማዕድን ዘርፉን ገቢ አሳድጓል ተባለ

By yeshambel Mihert

January 28, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለማዕድን ዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠቱ የዘርፉን ገቢ ማሳደጉን የኦሮሚያ ማዕድን ልማት ባለስልጣን ገለጸ፡፡

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ነመራ ገበየሁ (ዶ/ር) ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት÷በዘርፉ የነበሩ ችግሮችን በመቅረፍ ጥሩ ውጤት እየተገኘ ነው፡፡

በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት 3 ሺህ 929 ኪሎ ግራም ወርቅ ወደ ብሄራዊ ባንክ የተላከ ሲሆን÷ ከ385 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱንም ተናግረዋል፡፡

የማዕድን ግብይትን በማሻሻል በሀገር ውስጥ ገበያም ከ1 ቢሊየን ብር በላይ መገኘቱን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የከሰል ድንጋይን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት ከ26 ሚሊየን ዶላር በላይ ወጪን ማዳን መቻሉን እንዲሁም ከ47 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ እድል መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡

በማርታ ጌታቸው