የሀገር ውስጥ ዜና

የክልሉን የንጹህ መጠጥ ውኃ ሽፋን በ2 ነጥብ 18 በመቶ ለማሳደግ እየተሠራ ነው

By ዮሐንስ ደርበው

January 29, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ነባርና አዳዲስ የመጠጥ ውኃ ተቋማት ግንባታን በማከናወን የክልሉን የንጹህ መጠጥ ውኃ ሽፋን በ2 ነጥብ 18 በመቶ ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑን የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ማማሩ አያሌው (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ግቡን ለማሳካትም በበጀት ዓመቱ 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ከመንግሥት መደበኛ በጀት፣ ከ900 ሚሊየን ብር በላይ ከአንድ ዋሽ ብሔራዊ ፕሮግራም እና ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ከፌደራል መንግሥት መመደቡን አብራርተዋል፡፡

በአጠቃላይ ከ3 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በሚልቅ ወጪ በተያዘው የበጀት ዓመት የክልሉን የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ተደራሽነት የማሳደግ ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡

በመልሶ ማቋቋም ለሚጠገኑ የውኃ ተቋማት 70 ሚሊየን ብር መመደቡን እና በአብዛኛው በግዥ ሂደት ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

24 የከተማ ፕሮጀክቶች እና 34 የገጠር መንገድ አገናኝ ፕሮጀክቶችን በዚህ ዓመት ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ነው ኃላፊው ለፋና ዲጂታል የገለጹት፡፡

ነባር እና አዲስ የመጠጥ ውኃ ተቋማት ግንባታን በማከናወን የክልሉን የንጹህ መጠጥ ውኃ ሽፋን በዚህ ዓመት በ2 ነጥብ 18 በመቶ በማሳደግ አጠቃላይ ሽፋኑን 77 ነጥብ 45 በመቶ ለማድረስ የተቀናጀ ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡

በግንባታ ላይ ከሚገኙት የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች መካከል 58ቱን በዚህ ዓመት በማጠናቀቅ 519 ሺህ 620 የሕብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ይገኛልም ነው ያሉት፡፡

ባለፉት ሥድስት ወራት በገጠር ሁለት ቀበሌ አገናኝ ፕሮጀክት በከተማ ሦስት የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት በማጠናቀቅ 73 ሺህ 796 የሕብረተሰብ ክፍሎችን የንጹህ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡

በተጨማሪም ዶዶ፣ አባመላ፣ ጨፋ ሮቢት፣ ወይንአምባ፣ ቢቸና እና ሰኞ ገበያ የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶችም ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ከተጠናቀቁት መካከል መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

ከዚህ በፊት ተገንብተው በኃይል አቅርቦት ችግር በሙሉ አቅማቸው አገልግሎት የማይሰጡ ተቋማትን የኃይል አማራጭ ወደ ፀሐይ ኃይል የመቀየር ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው