የሀገር ውስጥ ዜና

የድንገተኛና ጽኑ ሕሙማን ሕክምና አገልግሎትን ለማጠናከር እየተሰራ ነው

By Melaku Gedif

January 29, 2025

አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የድንገተኛና ጽኑ ሕሙማን ሕክምና አገልግሎትን ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

የጤና ሚኒስትር ዴዔታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፥ በኢትዮጵያ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ለድንገተኛና ጽኑ ሕመም ለሚጋለጡ ዜጎች ደረጃውን የጠበቀ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት በትኩረት እየተሰራ ነው።

አገልግሎቱ ፈጣን ምላሽ ሰጪ የጤና ስርዓትን በመገንባት የዜጎችን ሞትና አካል ጉዳት ለመቀነስ እንደሚያስችል አመልክተዋል።

አሁን ላይ የድንገተኛና ጽኑ ሕሙማን አገልግሎት ደረጃ እየተሻሻለ መምጣቱን ጠቁመው፥ በቀጣይ አገልግሎቱን ለማጠናከር በዘርፉ በቂ ባለሞያዎችን ማፍራት ይገባል ብለዋል።

ለዚህም ጤና ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ድንገተኛና ጽኑ ሕሙማን ሕክምና ባለሞያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ዶ/ር ወልደሰንበት ዋጋኖ በበኩላቸው ፥ ማህበሩ በተለያዩ አደጋዎች ሳቢያ ለጽኑ ሕመም ለተዳረጉ ዜጎች አገልግሎት እየሰጠ ነው ብለዋል።

በዚህም በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ 30 በላይ ድንገተኛ እና 119 የጽኑ ሕሙማን ክፍሎች ላይ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።

የማህበሩ አባላት ያላቸውን ልምድ እና ተሞክሮ በመጠቀም በጽኑ ታካሚዎች ዘርፍ ጥናትና ምርምር እንደሚያደርጉ ጠቅሰው፤ አገልግሎቱን ይበልጥ ለማሻሻል አጋሮች ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በመላኩ ገድፍ