አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሩዋንዳ ኪጋሊ የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት 26ኛው ጠቅላላ ጉባኤ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በጉባኤው የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል እየተሳተፉ መሆኑ ተገልጿል።
ጉባኤው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በቀጣናው ከሚገኙ የፖሊስ ተቋማት ጋር በትብብር ለመስራት ወሳኝ ዕድል የሚፈጥርለት መሆኑም ተመላክቷል።
ድርጅቱ በቀጣናው የሚገኙ የፖሊስ ተቋማትን በማስተሳሰር በተባበረ ክንድ የተደራጁ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል ወሳኝ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ መገለጹን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመለክታል።
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ በጉባዔው ላይ እንዳሉት÷ አፍሪፖልን ማጠናከር የአፍሪካ የፖሊስ ተቋማት በዓለም መድረክ ላይ ያላቸውን ሚና ያሳድጋል፡፡
ስለሆነም ሁሉም የቀጣናው አባል ሀገራት ተቋሙን ለማጠናከር በትብብር መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል።
የኮሚሽነር ጀነራሉ ሐሳብ በድርጅቱ አባል ሀገራት ከፍተኛ ድጋፍ ማግኘቱም ነው የተገለጸው፡፡